Aman Properties blog

From the
Aman blog

Guidesአማርኛ

የአዲስ አበባ ሰፈሮች እና ስያሜያቸው

3 November 2026 · 3 min read · Aman Properties

እኛ ኢትዮጵያውያን ለሰውም ሆነ ለቦታ ስም ስናወጣ እንዲሁ በዋዛ አይደለም። ከአንድ አጋጣሚ ወይም ሁነት ጋር የተገናኙ ፤ ከበስተጀርባቸው የራሳቸው ምክንያት ያላቸው ስያሜዎችን ማውጣት ልማዳችን ነው።

የከተሞችን ስያሜ እንደ ምሳሌ ወስደን ብንመለከት እንኳ በጣና ሐይቅ ዳርቻ ላይ የተቆረቆረችውን ከተማ ባህር ዳር ፤ 40 ምንጮች የከበቧትን ከተማ አርባምንጭ ፤ ሜዳማዋን ከተማ ደግሞ ድሬ ዳዋ ወይም ሰፊ ሜዳ እያልን ወይ ከአየር ሁኔታቸው ጋር ወይ ከመልክዓ ምድራቸው ጋር እና በጊዜው ከተፈጠረ ታሪካዊ ሁነት ጋር በማገናኘት ስያሜዎችን እንሰጣለን።

ዛሬ ርዕሳችን ልናደርጋት ወደ መረጥናት አዲስ አበባ እንምጣ!

ሳር ቤት ፣ ፒያሳ ፣ ቦሌ ፤ ካዛንቺስ ፣  ካዛ ፖፖላሬ ፤ መርካቶ ፤ ሽሮ ሜዳ ፣ አራት ፣ አምስት ፣ ስድስት ኪሎ ፣ አዋሬ ፣ ሉካንዷ ፣ ሌላም ሌላም ሰፈሮች አሏት አዲስ አበባ።

አጼ ሚኒሊክ እና እቴጌ ጣይቱ ብጡል የእንጦጦ ብርድ ቢከብዳቸው ወደ ፍል ውሃ  ወርደው በሰፈሩበት ወቅት የተቆረቆረችው አዲስ አበባ ፤ የንግስቲቱን ቀልብ በማረከችው እና አይተዋት በማያውቋት ልዩ እና አዲስ አበባ አማካኝነት ስያሜዋን እንዳገኘች ይነገርላታል።

በ1879 የተመሰረተችው እና የንጉሱን ቤተሰብ እና አጀብዎች ብቻ ይዛ የነበረችው አዲስ አበባ ፤ ዛሬ በሚሊየን የሚቆጠሩ ህዝቦችን አቅፋ የያዘች ሰፊ እና ውብ ከተማ ሆናለች ።  በአራቱም አቅጣጫ በተለያዩ ሰፈሮች የተከፋፈለች ፣ ከኢትዮጵያ መዲና ወደ አፍሪካ መዲናነት የተሸጋገረች ፤ ከአለም የተውጣጡ እንግዶችን የምታስተናግድ ዝነኛ እና ዘመናዊ ከተማ ነች አዲስ አበባ።

የሚገርመው ግን የሰፈሮቿ ስያሜም ልክ እንደ ከተማዋ ሁሉ አለም አቀፍ ይዘት ያለው መሆኑ ነው።

ሜክሲኮ ፣ ጃፓን ፣ ፈረንሳይ ፣ ቡልጋሪያ ፣ ጀርመን ፣ ኮሪያ የመሳሰሉ ከባህር ባሻገር ባሉ ከተሞች ስም የተሰየሙ ስፈሮች ያሏት ሲሆን ፤ በጣሊያን ወረራ ወቅትም የተሰየሙ እንደ መርካቶ ፤ ፒያሳ ፤ ካዛንቺስ እና ካዛ ፖፖላሬ አይነት ቦታዎች አሏት ።

ዛሬ እነዚህ ሰፈሮች እንዴት ተሰየሙ? ማንስ ሰየማቸው የሚለውን ካዛንቺስን ቀዳሚ አድርገን የሶስቱን ታሪክ በአጭሩ እንመልከታለን፦

ካዛንቺስ፡ አዲስ አበባ በአጼ ሚኒሊክ እና በእቴጌ ጣይቱ ከተቆረቆረች ከግማሽ ክፍለ ዘመን ገደማ በኋላ በጣሊያን ወረራ ወቅት (ከ1928 - 1933 ዓ.ም) ስያሜያቸውን ካገኙ ሰፈሮች አንዱ ካዛንቺስ ነው።

በወቅቱ ጣሊያን ለመንግስት ሰራተኛ ዜጎቿ መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት INCIS (ኢንቺስ) የተባለ የመንግስት ተቋም ነበራት። በዚህ ተቋም የሚገነቡት የመኖሪያ ቤቶችም በጣሊያንኛ “Casa INCIS” (የኢንቺስ ቤቶች) ተብለው ይጠሩ ነበር፤ “ካዛ” ማለት በጣሊያንኛ “ቤት” ማለት ነው።

በጊዜ ሂደት የከተማው ነዋሪ “ካዛ ኢንቺስ” ን  “ካዛንቺስ” እያለ መጥራት ጀመረ። ሰፈሩም ከዚህ የተነሳ ስያሜውን አገኘ። 

ሳር ቤት፡ በአጼ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት እንደ ከተማ ዳርቻ በሚቆጠረውና ጥቂት ህዝብ ብቻ ይኖርበት በነበረው አካባቢ፣ ሁለት ግዙፍ የሳር ክዳን ቤቶች ጎልተው ይታዩ ነበር። ቀስ በቀስ ታዲያ አገሬው እነዚያን ሳር ቤቶች እንደ ምልክት በመውሰድ “ሳር ቤቱ ጋር ነኝ” ፣ “ሳር ቤቱ ጋር ጠብቀኝ” እያለ ቦታ ለመጠቋቆም ይጠቀምበት ጀመረ። ውሎ እያደር ሳር ቤት የአካባቢው መጠሪያ ለመሆን በቃ።

ፒያሳ፡ ቃሉ “piazza” ከሚለው የጣሊያንኛ ቃል የተገኘ ሲሆን የህዝብ አደባባይ ወይም ክፍት የንግድ ስፍራ የሚል ትርጓሜ አለው። አዲስ አበባ ስትቆረቆር ከነበሩ ቀደምት የከተማዋ ሰፈሮች አንዱ ሲሆን የቀድሞ ስሙ አራዳ ነበር።  አራዳ ማለት በወቅቱ የገበያ እና የከተሜነት መገለጫ የነበረ ሥፍራ ነው።

ፋስሽት ጣሊያን ኢትዮጵያን ወርሮ በቆየበት የ5 አመት ቆይታ ግን ጣሊያኖች አካባቢውን የአስተዳደር እና የንግድ ማዕከል አድርገውት የነበረ ሲሆን በወቅቱም የጣሊያንን አርክቴክቸር፣ ካፌዎች እና ሱቆች በመገንባት ሥፍራውን በቋንቋቸው "Piazza" (ፒያሳ) ብለው መጥራት ጀመሩ።

ፋስሽት ጣሊያንን ድል ነስተን ካባረርነው ድፍን 80 አመት ያለፈን ቢሆንም ስያሜው የሰው ልብ ውስጥ ቀርቶ ነበርና ዛሬም ድረስ አራዳ “ፒያሳ” በሚለው ስያሜ ጸንቷል።     

ሁሉንም የአዲስ አበባ ሰፈሮች ስያሜ እና አመጣጥ በአንድ ጦማር ለመጻፍ ያለን ጊዜ ስለሚገድብን ለዛሬው በዚህ እናበቃለን። በክፍል ሁለት በሌላ የአዲስ አበባ ስያሜ እና ታሪክ እንመለሳለን።

በአማን ውላችሁ ፤ በአማን እደሩ!

አማን ፕሮፐርቲስ

ንብረትዎን በአስተማማኝ እጆች! 

← All articles

We are open

Talk to us today

Call, message or visit the sales office at Laphto Mall — we reply the same working day.

Call us
+251 945 59 59 59
Call short code
8077
WhatsApp
Message us
Email
info@amanpropertiesaddis.com
☎Call ✉WhatsApp ✎Book